የ2019 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ውድድር በአምስት ጨዋታዎች ሲቀጥል፣ አራቱ በ1 ለ 0 ውጤት ተጠናቀዋል። በቀሪው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ጋሞ ጨንቻን 2 ለ 0 አሸንፏል። ከውጤቶቹ ባሻገር ግን የሀዲያ ሆሳዕና የሜዳው ጅማሮ፣ የመቻል የሁለተኛ አጋማሽ እንቅስቃሴ፣ የኢትዮጵያ ቡና የማጥቃት ክፍተቶችና የመጫወቻ ሜዳዎች ጥራት የዕለቱ ዋና የውይይት ርዕሶች ሆነዋል።
ሀዲያ ሆሳዕና፦ የስድስት ዓመታት በሜዳው የመጫወት ጥበቃን ያልመጠነ ጅማሮ
ሀዲያ ሆሳዕና 0–1 ባህር ዳር ከተማ
ከስድስት ዓመታት ጥበቃ በኋላ ወደ ሜዳው የተመለሰው ሀዲያ ሆሳዕና፣ የደጋፊዎቹን ታላቅ ጉጉት የሚመጥን እግር ኳስ ማሳየት አልቻለም። በዚህ ጨዋታ ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች አንዱ የአዲሱ አሰልጣኝ የተጫዋቾች ምርጫ ነው። በመጀመሪያ አሰላለፉ ዘጠኝ አዲስ ፈራሚዎችን ሲያካትት፣ በክለቡ የወጣት ቡድን ያደጉና ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሊጉ በመጫወት ልምድ ያካበቱ ተጫዋቾችን አልመረጠም። ይህ ውሳኔ ከክለቡ የባለፉት ዓመታት ባህልና ጨዋታው በሜዳቸው ከረጅም ጊዜ በኋላ ከመደረጉ አንፃር ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ሀዲያ ሆሳዕና የአካባቢውን ወጣቶች በማሳደግና ለዋናው ቡድን በማብቃት የሚታወቅ ክለብ ነው። እነዚህ ተጫዋቾች በቤተሰቦቻቸውና በጓደኞቻቸው ፊት መጫወታቸው ተጨማሪ ተነሳሽነት ሊሰጣቸው፣ የደጋፊዎችንም ከቡድኑ ጋር ያላቸውን ትስስር ሊያጠናክር ይችል ነበር።
በእርግጥ አሰልጣኝ ተጫዋቾችን በብቃት፣ በዝግጁነትና በታክቲክ ፍላጎት መሠረት የመምረጥ መብትና ኃላፊነት አለበት። አዲስ ፈራሚዎችን ማሰለፍም በራሱ ስህተት አይደለም። የዕለቱን ሽንፈት በአሰላለፍ ምርጫው ብቻ ማሳሰብ ባይቻልም፣ በአዲስ ፈራሚዎችና ከታች አድገው በክለቡ አብረው የቆዩ ተጫዋቾችን በማዋሃድ የተሻለ ሚዛን መፍጠር ለቀጣይ ጉዞው ቁልፍ ጉዳይ ይሆናል።
መቻል፦ የሁለተኛው አጋማሽ እንቅስቃሴና የሜዳው ፈተና
ሀዋሳ ከተማ 0–1 መቻል
መቻል ሀዋሳ ከተማን ከሜዳው ውጪ 1 ለ 0 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በሦስት ነጥብ ጀምሯል። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ያሳየው የኳስ እንቅስቃሴ ከዕለቱ አዎንታዊ ጎኖች አንዱ ነበር። በቅብብል፣ በቦታ አያያዝና በማጥቃት ሂደት የተሻለ ቅንጅት ያሳየው መቻል፣ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ ሁኔታ ቢያስቸግረውም የጨዋታ አቀራረቡን ለመጠበቅ ሞክሯል።
በእርግጥ ሀዋሳ ከተማ የመቻልን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመግታት ቢሞክርም፣ በሁለተኛው አጋማሽ ለመቻል ከተጋጣሚው የመከላከል አቅም ይልቅ የሜዳው ጥራት የበለጠ ለአጨዋወቱ እንቅፋት ሆኖበት ታይቷል። በአጭር ቅብብልና በፈጣን የኳስ ዝውውር ላይ የተመሠረተ እግር ኳስ ለመጫወት ተስማሚ ሜዳ ወሳኝ መሆኑን የመቻል የዕለቱ እንቅስቃሴ በግልጽ አሳይቷል።
ኢትዮጵያ ቡና፦ የማጥቃት ቅንጅት እጥረት
ኢትዮጵያ ቡና 0–1 ሸገር ከተማ
ኢትዮጵያ ቡና በሸገር ከተማ 1 ለ 0 ተሸንፎ የውድድር ዓመቱን ጀምሯል። የቡናማዎቹ ዋና ችግር ኳሱን ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ማድረስ ሳይሆን፣ ወደ ግብ ክልል ሲቃረቡ የሚያሳዩት የቅንጅት እጥረት ነበር። በተለይ በሦስቱ የፊት አጥቂዎች መካከል የሚጠበቀው መናበብ አልታየም። የቦታ ለውጥ፣ የተጫዋቾች ከኳስ ውጪ እንቅስቃሴና የመጨረሻ ቅብብል ውሳኔዎች በቂ ቅንጅት አላሳዩም። በዚህም ምክንያት ቡድኑ ወደ ፊት የሚያደርገውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ግልጽ የግብ ዕድል መቀየር ተቸግሮ ውሏል።
በአንፃሩ ሸገር ከተማ ወደ ፊት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የበለጠ የማሸነፍ ፍላጎት ያሳየ ሲሆን፣ በርካታ ግልጽ የግብ ዕድሎችንም ፈጥሯል። ጥረቱም በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ፍሬ አፍርቶ፣ ካሌብ በየነ ከቅጣት ምት ባስቆጠረው ግብ አሸናፊ ሆኗል። በዚህም ሸገር ከተማ ከሜዳው ውጪ ሦስቱን ነጥቦች ይዞ መውጣት ችሏል።
ኢትዮጵያ መድንና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በድል ጀምረዋል
ጋሞ ጨንቻ 0–2 ኢትዮጵያ መድን
ኢትዮጵያ መድን ጋሞ ጨንቻን 2 ለ 0 በማሸነፍ በሳምንቱ ከአንድ በላይ ግብ ያስቆጠረ ብቸኛው ቡድን ሆኗል። ይህም ከሌሎች የሳምንቱ አሸናፊዎች በተሻለ የግብ ልዩነት የውድድር ዓመቱን እንዲጀምር አስችሎታል።
ሲዳማ ቡና 0–1 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
የአምናው ሻምፒዮን ሲዳማ ቡና የዋንጫ ክብሩን የማስጠበቅ ጉዞውን በሽንፈት ጀምሯል። በአንፃሩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሻምፒዮኑ ሦስት ነጥብ ከሜዳው ዉጭ ማግኘቱ በመጀመሪያው ሳምንት ትኩረት ከሳቡ ውጤቶች አንዱ ሆኗል።
የመጫወቻ ሜዳዎች ጥራት፦ የሊጉ ትልቁ ፈተና መሆኑ በዚህ አመትም ቀጥሎዋል
የዕለቱ ጨዋታዎች ዳግም ያስታወሱት አሳሳቢ ጉዳይ የመጫወቻ ሜዳዎች ጥራት ነው። በአዲስ አበባ ስታዲየም፣ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየምና በአብዩ ኤርሳሞ ስታዲየም ያሉ የሜዳ ችግሮች የእግር ኳሱን ጥራት እየጎዱ ነው። ኳስ በማይጠበቅ አቅጣጫ የሚነጥርበት፣ ቅብብልን የሚያስተጓጉልና የተጫዋቾችን እንቅስቃሴ የሚገድብ ሜዳ ጥራት ያለው እግር ኳስ ለማየት ትልቅ ፈተና ነው። በተለይ በአጭር ቅብብልና በፈጣን የኳስ ዝውውር ለመጫወት የሚሞክሩ ቡድኖች በዚህ ከማንም የበለጠ ተጎጂ ናቸው።
ክለቦች በተጫዋቾችና በአሰልጣኞች ላይ ከፍተኛ ወጪ እያደረጉ ሳለ፣ የመጫወቻ ሜዳዎቻቸውን በተመሳሳይ ደረጃ ካልሻሻሉ የሊጉን ጨዋታ ጥራት ማሳደግ አስቸጋሪ ይሆናል። የሊጉ አዘጋጆች የሜዳዎችን ሁኔታ በድጋሚ መገምገምና ለጨዋታ ተስማሚ የሆነ ደረጃ እንዲጠበቁ ማድረግ አሁንም ይጠበቅባቸዋል።
የዕለቱ ጨዋታዎች ምን አስመለከቱ?
የመጀመሪያው ሳምንት አምስት ጨዋታዎች ከውጤት በላይ የሚታዩ በርካታ ጉዳዮችን አስተናግደዋል። ሀዲያ ሆሳዕና የክለቡን ማንነት ከአዲሱ የቡድን ግንባታ ጋር የማስማማት ፈተና ተጋርጦበታል። መቻል በሁለተኛው አጋማሽ አበረታች እንቅስቃሴ ሲያሳይ፣ ኢትዮጵያ ቡና የማጥቃት ቅንጅቱን ማሻሻል እንዳለበት አሳይቷል። ኢትዮጵያ መድንና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ውድድሩን በድል ጀምረዋል።
የሊጉ የረጅም ጊዜ እድገት ግን ክለቦች ተጫዋቾችን በዉድ ዋጋ ማዘዋወር ላይ ብቻ ያትኮረ ሳይሆን፣ የቡድን ግንባታ፣ የወጣቶች ልማትና የመጫወቻ ሜዳዎች ጥራት አብረው ሲሻሻሉ ብቻ ነው በሜዳ ላይ የሚታየው እግር ኳስ ወደ ተሻለ ደረጃ ሊደርስ የሚችለው።
