የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ከነአን ማርክነህ ከሴኔጋል ጋር ነገ ለሚደረገው ጨዋታ ቡድኑ በጥሩ መንፈስ ዝግጅቱን እያደረገ መሆኑን ተናገረ።

ከነአን ከጨዋታው በፊት ለጋዜጠኞች በሰጠው ሀሳብ፣ ብሔራዊ ቡድኑ በባህር ዳር ስታዲየም ለመጨረሻ ጊዜ ከተጫወተ አምስት ዓመታት ማለፉን ጠቅሶ፣ ቡድኑ በዚህ ስታዲየም ሲጫወት ብዙ የሽንፈት ታሪክ እንደሌለው ገልጿል። ይህም በነገው ጨዋታ ለተጫዋቾቹ የስነ ልቦና ጥንካሬ እንደሚሰጥ ተናግሯል።

በሱዳን ጨዋታ ቡድኑ ያገኛቸውን የግብ ዕድሎች አለመጠቀሙን በተመለከተም፣ ከሱዳኑ ጨዋታ በኋላ እስከ ሴኔጋሉ ጨዋታ ያለው የዝግጅት ጊዜ አጭር በመሆኑ ብዙ ለውጦችን ለማድረግ ዕድል እንዳልነበረ ገልጿል። ሆኖም ቡድኑ ለነገው ጨዋታ በተሻለ የስነ ልቦና አቀራረብ መዘጋጀቱን ተናግሯል።

ከሱዳን ሽንፈት በኋላ ጠንካራውን የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ስለመግጠም እና የሜዳ ጥቅምን ስለመጠቀም ሲናገርም፣ ቡድኑ በባህር ዳር ያለው መልካም ታሪክ ለተጫዋቾቹ ተጨማሪ የስነ ልቦና ጥንካሬ እንደሚሆን አስረድቷል።

በመጀመሪያው ጨዋታ በሱዳን መሸነፋቸውን ተከትሎ ደጋፊዎች ድል እንደሚጠብቁ እና ይህም በተጫዋቾቹ ላይ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ሲጠየቅ፣ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የሚጫወት ተጫዋች ጫና መቋቋም መቻል እንዳለበት ከነአን ተናግሯል። እሱና የቡድን አጋሮቹም ይህንን ጫና መቋቋም እንደሚችሉ እምነቱን ገልጿል።

በሱዳን ጨዋታ ከተለመደው የተለየ ቦታ ላይ ስለመጫወቱም፣ በሜዳ ላይ እስካለ ድረስ በየትኛውም ቦታ መጫወት ችግር እንደሌለበት ተናግሯል። እግር ኳስ መጫወት ከቻልክ በሜዳ ላይ በተለያዩ ቦታዎች መጫወት እንደሚቻልም ገልጿል።

በመጨረሻም የባህር ዳር ደጋፊዎች ለእግር ኳስ ያላቸውን ፍቅር እንደሚያውቅ ገልጾ፣ ነገ ወደ ስታዲየም በመምጣት ብሔራዊ ቡድኑን እንደተለመደው እንዲደግፉ ጥሪ አቅርቧል።