የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን በ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ J ሁለተኛ ጨዋታውን ከኢትዮጵያ ጋር ለማድረግ ባህር ዳር የገባ ሲሆን፣ ዋና አሰልጣኙ ፓትሪክ ቪዬራ ከተወሰኑ ተጫዋቾቹ ጋር በመሆን ከጨዋታው በፊት ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሴኔጋል በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ ከሞዛምቢክ ጋር 1-1 በሆነ ውጤት ነጥብ ተጋርቶ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ሲሆን፣ ቪዬራ ቡድናቸው በባህር ዳር ሶስት ነጥብ ማግኘት ዋነኛ ዓላማው መሆኑን ገልጸዋል።
“ነገ የምንጫወተው ለሶስት ነጥብ ነው።” ያሉት ቪዬራ፣ ከመጀመሪያው ጨዋታ የተገኘው አንድ ነጥብ ቡድናቸው በቀጣዩ ጨዋታ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብ ያለውን ጫና እንደጨመረ አመልክተዋል።
ሱዳን የመጀመሪያውን የምድብ ጨዋታ በማሸነፍ የምድቡን ጉዞ በሶስት ነጥብ ከጀመረች በኋላ፣ ሴኔጋል በኢትዮጵያ ላይ ድል በማስመዝገብ በምድቡ ያለውን አቋም ለማጠናከር ይፈልጋል።
ቪዬራ ለኢትዮጵያ ቡድን ክብር ሰጥተዋል
ፈረንሳዊው አሰልጣኝ በጋዜጣዊ መግለጫቸው የኢትዮጵያን ቡድን አቅም አቅልለው እንደማይመለከቱት ገልጸው፣ ተጋጣሚያቸውን “የተደራጀና ሚዛኑን የጠበቀ ቡድን” ሲሉ ገልጸውታል።
“ለኢትዮጵያ ትልቅ ክብር አለን። የተደራጀ እና ሚዛኑን የጠበቀ ቡድን ነው የምንገጥመው።” ብለዋል።
ቪዬራ ኢትዮጵያ በራሷ ሜዳ ጨዋታውን ለሴኔጋል ከባድ ለማድረግ እንደምትሞክር እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።
“ጨዋታችንን ለማክበድ የሚሞክር ቡድን ነው የምንገጥመው። እኛም በሜዳ ላይ እንደምንሻል ማሳየት እንፈልጋለን።” ሲሉ አክለዋል።
ከሞዛምቢኩ ጨዋታ በኋላ የታክቲክ ማስተካከያ
ሴኔጋል ከሞዛምቢክ ጋር ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ለረጅም ጊዜ የኳስ ቁጥጥርና የጨዋታ ብልጫ ቢኖረውም፣ በተወሰኑ የጨዋታው ወቅቶች የታየው የትኩረት መቀነስ ተጋጣሚው ወደ ጨዋታው እንዲመለስ ዕድል ሰጥቶታል።
ቪዬራም ከኢትዮጵያ ጋር በሚደረገው ጨዋታ እነዚህን ድክመቶች ማስተካከል ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጠው አስረድተዋል።
የተጫዋቾች ሽክርክር ሊኖር ይችላል
ሴኔጋል በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሞዛምቢክ ወደ ኢትዮጵያ ረዥም ጉዞ ያደረገ መሆኑና በጥቂት ቀናት ልዩነት ሁለት ጨዋታዎችን ማድረጉ የተጫዋቾችን አካላዊ ብቃት በቅርብ እንዲገመግሙ አድርጓል።
ቪዬራ በአሰላለፋቸው ላይ የተወሰነ ለውጥ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ፍንጭ የሰጡ ሲሆን፣ ቡድናቸው አሁንም ከፍተኛ መነሳሳት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሳዲዮ ማኔ በቡድኑ ውስጥ በሌለበት ሁኔታ፣ ኒኮላስ ጃክሰን እና ኢሊማን ንዲያዬን ጨምሮ የሴኔጋል የጥቃት ተጫዋቾች በባህር ዳሩ ጨዋታ የበለጠ ኃላፊነት እንዲወስዱ ይጠበቃል።
የባህር ዳር ስታዲየምን አድንቀዋል
የሴኔጋል ቡድን ከማፑቶ ወደ ባህር ዳር በሁለት ቡድን ተከፍሎ የደረሰ ሲሆን፣ ቪዬራ በደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለቡድናቸው ለተደረገው አቀባበል ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
አሰልጣኙ የባህር ዳርን የአየር ንብረትና የስታዲየሙን የመጫወቻ ሜዳ ሁኔታም አድንቀዋል።
“የባህር ዳር ስታዲየም ሜዳው በጣም ጥሩ ሜዳ ነው። በጥሩ ስታዲየምና በጥሩ የመጫወቻ ሜዳ ላይ ነው የምንጫወተው፤ ይህ ለእኛ ጥሩ ነገር ነው።” ብለዋል።
ሴኔጋል ከጋዜጣዊ መግለጫው በኋላ በባህር ዳር ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዱን በማድረግ የጨዋታ ዝግጅቱን ያጠናቅቃል።
በአንፃሩ ኢትዮጵያም በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ ከሱዳን በ1-0 ከተሸነፈች በኋላ በሜዳዋ የመጀመሪያ ነጥቦቿን ለማስመዝገብ ወደ ጨዋታው ትገባለች። በመሆኑም የባህር ዳሩ ፍልሚያ ለሁለቱም ቡድኖች በምድቡ የቀጣይ ጉዞ ላይ ጠቃሚ የሆኑ ነጥቦችን የሚያስገኝ ወሳኝ ጨዋታ ይሆናል።
