አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመርማን ስለ ዩጋንዳው ጨዋታ፣ ስለተከተሉት ታክቲክ፣ ስለተጫዋቾቹ ብቃትና ስለውድድሩ አዘገጃጀት የተናገሩት
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመርማን ቡድናቸው ከዩጋንዳ ጋር 1 ለ 1 ከተለያየበት ጨዋታ በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ ለጨዋታው የተከተሉትን ታክቲካዊ አቀራረብ፣ የተጫዋቾቻቸውን አካላዊ ዝግጁነት፣ የእረፍት ጊዜ እጥረትንና የውድድሩን አዘገጃጀት በዝርዝር አብራርተዋል።
ስለ ጨዋታው ታክቲካዊ አቀራረብ
«ጨዋታው እጅግ ታክቲካዊ ነበር። በቂ የእረፍት ጊዜ ስላልነበረን የተለየ ውሳኔ መውሰድ ነበረብን። የምንገጥመው ቡድን አራት ቀናት ያረፈ ሲሆን፣ እኛ ግን ሁለት ቀናት እንኳን አልነበሩንም። በእርግጥ ከሁለት ቀናት ያነሰ የእረፍት ጊዜ ነበረን። በመደበኛው አሰራር ቢያንስ 48 ሰዓታት እረፍት ሊኖር ይገባል። እኛ ግን ያረፍነው 46 ሰዓታት ብቻ ነበር። ይህም በቡድናችን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ነበረው። ስለዚህ ከተለመደው የተለየ አጨዋወት መከተል እንዳለብን ተረድተን ነበር።
የዩጋንዳውን አሰልጣኝ በጣም አከብራለሁ። በተጫዋችነት ዘመናቸው የነበራቸውን ታሪክ አውቃለሁ። በአሰልጣኝነት ሲሰሩም ተከታትያቸዋለሁ፣ ስለእሳቸውም መረጃ ሰብስቤ ነበር። እጅግ ብልህና በታክቲክ የበሰሉ አሰልጣኝ ናቸው። ዩጋንዳ በጣም ጥሩ ቡድን አላት። በእኔ እምነት ዩጋንዳ በእግር ኳስ ልማት ፕሮጀክቷ ከእኛ በአስር ዓመታት ያህል ቀድማ ትገኛለች። እኛ የራሳችንን ፕሮጀክት በተግባር የጀመርነው ባለፈው ዓመት ነው። አሁን በሁለተኛ ዓመታችን ላይ እንገኛለን። ስለዚህ የተጋጣሚያችንን ብቃት ማክበርና በጥንቃቄ የተዘጋጀ ታክቲካዊ እቅድ መንደፍ ነበረብን። የዩጋንዳ ተጫዋቾች ከፍተኛ ፍጥነት አላቸው። ከተከላካዮቻችን ጀርባ ያለውን ክፍት ቦታ በመጠቀም እና በአጫጭር ቅብብሎች ተቀናጅተው በመጫወት አደጋ መፍጠር ይችላሉ። ይህንን በመረዳት የተለየ የጨዋታ አቀራረብ መረጥን። በመጨረሻም የተከተልነው እቅድ ውጤታማ እንደነበር አምናለሁ።»
ስለ ዩጋንዳ ተጫዋቾች አካላዊ ጥንካሬ ብልጫና የእረፍት ጊዜ
«የዩጋንዳ ቡድን ከእኛ በአካላዊ ብቃት ይበልጣል ከተባለ፣ በዚህ ሐሳብ አልስማማም። እነዚህን ተጫዋቾች ከያዝኳቸው ገና አስር ቀናት ብቻ ነው። ተጫዋቾቹም ከክረምት እረፍት ተመልሰው ነው ወደ ዝግጅት የገቡት። ነገር ግን ዩጋንዳውያን በአጠቃላይ ከኢትዮጵያውያን በአካላዊ ብቃት የተሻሉ ናቸው ከተባለ፣ ይህንን ፈጽሞ አልቀበልም። ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት ሩጫ ዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደምነት ያላቸው አትሌቶች ያሏት ሀገር ናት። ከአገሪቱ በተለየያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ከደቡብም ሆነ ከሰሜን የመጡ የተለያዩ ሕዝቦች ያሏት፣ 130 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሀገር ናት። ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ከዩጋንዳውያን በአካላዊ ብቃት ያንሳሉ የሚለውን አልቀበልም። ዋናው ነገር ታዲያ እኛ ምን አደረግን? እስከ መጨረሻው በከፍተኛ ትጋት ታገልን። ከሁኔታው ጋር የሚስማማ ታክቲካዊ እቅድም አዘጋጀን።
እንደገና ልናገር፣ ሴካፋ የሰጠን ሁለት ቀናት ብቻ የእረፍት ጊዜ ነው። ይህ ጨዋታ በመጀመሪያ ከሁለት ቀናት በፊት እንዲካሄድ የታቀደ ነበር። በዛሬው ምሽት ደግሞ ከቡሩንዲ ጋር መጫወት ነበረብን። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ፍጹም የተለየ ጨዋታ እንደሚሆን አረጋግጥላችኋለሁ። ሁለቱም ቡድኖች እኩል የእረፍት ጊዜ ባገኙበት ሁኔታ እንደገና ስንገናኝ፣ በእኩል ደረጃ መፎካከር እንደምንችል አምናለሁ። በቀጣይ እንደገና ከዩጋንዳ ጋር የምንጫወት ይመስለኛል።
ስለ ውድድሩ አዘገጃጀትና የሴካፋ ውሳኔዎች በምሬት ከተናገሩት
«እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህን መረጃዎች አስቀድመን ማግኘት ነበረብን። ሕጎቹና ደንቦቹ በጽሑፍ ተዘጋጅተው ሊሰጡን ይገባ ነበር። ስለእነዚህ ጉዳዮች አስቀድሞ የተወሰነ ደንብ ሊኖር ይገባል። አሁን ግን አዘጋጆቹ የሚወስኑትን ውሳኔ ለመጠበቅ ተገደናል። እኛ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋችንን በእርግጠኝነት አናውቅም ነበር። ነገር ግን ወደ ሜዳ የገባነው አቻ ለመውጣት አልነበረም። ለማሸነፍ ነበር የተጫወትነው። ዓላማችንም ይህ ነበር። አቻ መውጣት ወደ ቀጣዩ ዙር እንደሚያሳልፈን አናውቅም ነበር። ሆኖም እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ተጫዋቾቻችን ለድል ሲታገሉ ነበር። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከተጫዋቾቻችን አንዱ በድካም ምክንያት ኳሱን ለመንጠቅ በሸርተቴ ሲገባ በፈጸመው ጥፋት፣ ዩጋንዳዎች ግብ ሊያስቆጥሩብን ተቃርበው ነበር። እንደገና ዳኛው አምስት ተጨማሪ ደቂቃዎች ሰጠ። አምስት ሙሉ ደቂቃዎች! ይህን ያህል ተጨማሪ ጊዜ ይሰጣል ብሎ የጠበቀ ሰው አልነበረም።
ይህን የምለው ቅሬታ ለማቅረብ አይደለም። ያስተዋልኩትን ነገር እየተናገርኩ ነው። በምሥራቅ አፍሪካ መሥራት በጣም አስቸጋሪ ነው። አንዳንድ ነገሮች በድንገት ይቀየራሉ። ውሳኔዎችም ለእኛ ምንም ሳይነገረን ይወሰናሉ። ይህ ሁሉ ቢሆንም ልጆቹ አምበሶች ናቸው። ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ አምበሶች ናቸው! አሁን ከድካማችን ለማገገም እንሞክራለን። በቀጣይ ከማን ጋር እንደሚያጫውቱን እንጠብቃለን። ከዚያም ጉዟችን የት እንደሚደርስ እናያለን።»
ስለ ቡድኑ መንፈስ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙርና የደጋፊዎች ሚና
«አንድ ነገር ልናገር። የኢትዮጵያን ብሔራዊ መዝሙር በእንግሊዝኛ ተርጉሜ ለመማር ሞክሬያለሁ። አሁን ዜማውን ማንጎራጎር እችላለሁ። በተጫዋቾቼ በጣም እኮራለሁ። በአሰልጣኝ ቡዱኑ እና በድጋፍ ሰጪ ሠራተኞቻችንም እኮራለሁ። ሁሉም በከፍተኛ ትጋት እየሠሩ ነው። ሜዳ መጥተው ለሚደግፉን ኢትዮጵያውያንም ትልቅ ክብር አለኝ።
እኛ የምንታገለው ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያውያን እግር ኳስን ከልባቸው የሚወዱ ሕዝቦች ናቸው። ይህ ፍቅራቸውና ድጋፋቸው ወደፊት እንድንገፋ ትልቅ ኃይል ይሰጠናል። ለተጫዋቾቼ ሁልጊዜ የምነግራቸው አንድ ነገር አለ። የሕዝቡ ተስፋና ድጋፍ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ተጠቀሙበት እንጅ፤ ጫና ሆኖ ወደ ታች እንዲጎትታችሁ አትፍቀዱ።
ኢትዮጵያ፣ ቅዳሜ እንገናኝ። የምትችሉ ሁሉ መጥታችሁ ድጋፋችሁን አሳዩን።
