በ2019 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት የሰኞ ጥቅምት 16 ውሎ፣ ወላይታ ድቻ ሀላባ ከተማን 6 ለ 0 በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን ከፍተኛ የግብ ቁጥር አስመዝግቧል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሸገር ከተማ 2 ለ 2 ተለያይቶ የመጀመሪያ ድሉን ፍለጋው ሲቀጥል፣ ነገሌ አርሲ አዳማ ከተማን 1 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ሰንጠረዡ አናት ወጥቷል። ጋሞ ጨንቻና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ጊዮርጊስ በአዝናኝ ጨዋታ ነጥብ ተጋራ

በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስና ሸገር ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ክፍትና ማራኪ ፉክክር አስመልክቷል። በተለይ ሁለተኛው አጋማሽ፣ በወጣት ተጫዋቾች ዙሪያ የተገነቡት ሁለቱ ቡድኖች በፈጣን ሽግግርና ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተፎካከሩበት ነበር። ሸገር ከተማ በ29ኛው ደቂቃ በአሚር አብዶ ግብ መሪ ሆኖ ወደ ዕረፍት ቢሄዱም፣ ከዕረፍት መልስ ግን አማኑኤል ኤርቦ በ51ኛው ደቂቃ ጊዮርጊስን አቻ አድርጓል። ናትናኤል ዳንኤል በ73ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ግብ ፈረሰኞቹን ወደ መሪነት ቢያሸጋግርም፣ ይህን ብልጫ የያዙት ለስድስት ደቂቃዎች ብቻ ነበር። ቢንያም ፍቅሩ በ79ኛው ደቂቃ ለሸገር የአቻነት ግብ በማስቆጠር ጨዋታው 2 ለ 2 ተጠናቆዋል።

የጨዋታው ፍጥነትና የወጣቶቹ ተነሳሽነት ለተመልካች አሰደሳች የነበረ ቢሆንም፣ ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን ሦስት ነጥብ ለማግኘት የነበረው ጥረት አሁንም አልተሳካም። የሚቾ ቡድን ከአራት ጨዋታዎች ሦስት አቻና አንድ ሽንፈት በማስመዝገብ በሦስት ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፣ ሸገር ከተማ በበኩሉ በአምስት ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦዋል።

ነገሌ አርሲ በድል ወደ መሪነት

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ነገሌ አርሲ አዳማ ከተማን 1 ለ 0 በማሸነፍ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን ሲያስመዘግብ፣ የጨዋታውን ብቸኛ ግብ ዴሲሬ ፓስካል በ33ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል። ጨዋታው በሁለቱም ወገኖች የፍጹም ቅጣት ምት ቅሬታዎች የተነሱበትም ነበር። በሁለቱም የቅጣት ምት ክልሎች ውስጥ በተፈጸሙ ጥፋቶች ላይ የቀረቡት ጥያቄዎች ተገቢ ቢመስሉም፣ ዳኛው የፍጹም ቅጣት ምት ሳይሰጡ ማለፋቸው፣ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ቅሬታን ፈጥረዋል። ነገሌ የአንድ ጎል መሪነቱን እስከ መጨረሻው በማስጠበቅ ነጥቡን ስምንት አድርሷል። ከአራት ጨዋታዎች ሁለት ድሎችና ሁለት አቻዎች ያሉት ቡድኑ፣ ያለመሸነፍ ጉዞውን ቀጥሎ በግብ ልዩነት ንግድ ባንክን በመብለጥ የሊጉ መሪ ሆኗል። የመጀመሪያ ሽንፈቱን ያስተናገደው አዳማ በአምስት ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ጋሞ ጨንቻ የመጀመሪያ ነጥቡን አገኘ

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አባያ ካምፓስ ስታዲየም፣ ጋሞ ጨንቻ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ባስተናገደበት ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ያለ ግብ ተለያይተዋል። አዲስ አዳጊው ጋሞ ጨንቻ ከሁለት ሽንፈቶች በኋላ በሊጉ የመጀመሪያ ነጥቡን ቢያገኝም፣ በሜዳው የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ ሌላ ሳምንት ለመጠበቅ ተገዶዋል። ቡድኑ በአንድ ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በአንጻሩ ንግድ ባንክ ከሁለት ድሎች በኋላ ሁለተኛ ተከታታይ አቻውን አስመዝግቧል። ባንኮቹ ያለመሸነፍ ጉዟቸውን ቢቀጥሉም፣ በስምንት ነጥብ ከነገሌ አርሲ ጋር እኩል ሆነው በግብ ልዩነት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ወርደዋል።

ድቻ ስድስት የጎል ናዳ ሲያወረድ፤ መሳይ ሰለሞን የዓመቱን የመጀመሪያ ሦስትዮሽ አስቆጥሮዋል

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ሀላባ ከተማን 6 ለ 0 ያሸነፈበት፣ ከጅማሮው እስከ ፍጻሜው ክፍትና በጎል የታጀበ ጨዋታ ነበር። ድቻ የፈጠራቸውን ዕድሎች በወደጎል በመቀየር የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድል በሰፊ ውጤት አስመዝግቧል። ሱሌይማን ሀሚድ በ25ኛው ደቂቃ የግብ በሩን ሲከፍት፣ መሳይ ሰለሞን በ36ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ሁለተኛ ግብ ድቻን በሁለት ግብ መሪነት ወደ ዕረፍት ወስዶዋል። ከዕረፍት መልስም የድቻ የማጥቃት ሃይል ቀጥሎ፣ መሳይ ሰለሞን በ48ኛው ደቂቃ ለ ራሱ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር ውጤቱን 3 ለ 0 አድርሶታል። ቴዎድሮስ ታፈሰ በ55ኛው ደቂቃ አራተኛውን፣ ያኦቪ ጆሴፍ ደግሞ በ76ኛው ደቂቃ አምስተኛውን ግብ አክለው፣ በመጨረሻም መሳይ ሰለሞን በ88ኛው ደቂቃ ለራሱ ሦስተኛ ግቡንና የቡድኑን ስድስተኛ ጎል በማስቆጠር የዓመቱ የመጀመሪያ ሦስትዮሽ ባለቤት ለመሆን ችሎዋል። መሳይ በኢትዮጲያ ፕርሚየር ሊግ ከ 16 ወር ወይም ከ505 ቀናት በኋላ ሦስትዮሽ የሰራ ተጫዋች ሆኗል።

ድቻ ይህን ድል ያስመዘገበው የ10 ጨዋታዎች እገዳቸውን እያሳለፉ ያሉት ዋና አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ባልመሩት ጨዋታ ሲሆን፣ በምክትል አሰልጣኙ የተመራው ቡድን፣ በዘንድሮው ሊግ በአንድ ጨዋታ ከፍተኛውን የጎል ብዛት በማስቆጠር የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን በሚያስደንቅ የበላይነት አግኝቷል። ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ በአምስት ነጥብና በአራት የግብ ልዩነት ከ15ኛ ወደ ስድስተኛ ደረጃ ከፍ ሲል፣ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ያልተሸነፈው ሀላባ ከተማ ደግሞ የመጀመሪያ ሽንፈቱን በከባድ ውጤት ከሜዳው ዉጭ አስተናግዶ፣ በአምስት ነጥብ ወደ ዘጠነኛ ደረጃ ወርዷ።