የወላይታ ድቻ ዋና አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ፣ ቡድናቸው ከባህርዳር ከተማ ጋር ባደረገው የሦስተኛ ሳምንት ጨዋታ በፈጸሟቸው የዲሲፕሊን ጉድለቶች በድምሩ ከ10 ጨዋታዎች እንዲታገዱና 10 ሺህ ብር ቅጣት እንዲከፍሉ ተወሰነባቸው። ሐሙስ ጥቅምት 12 ቀን 2019 ዓ.ም. ከባሕር ዳር ቡድን ጋር በተደረገው ጨዋታ በ90+4ኛው ደቂቃ ዳኞችን በአጸያፊ ቃላት በመሳደባቸው በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግደዋል። ለዚህ ጥፋት የስድስት ጨዋታዎች እገዳና የአምስት ሺህ ብር መቀጮ ተጥሎባቸዋል።

አሰልጣኙ በቀይ ካርድ ከሜዳ በተወገዱበት ወቅት አራተኛውን ዳኛ ለመማታት መሞከራቸውን ለኮሚቴው የቀረበው ሪፖርት ይገልጻል። በዚህም ጨዋታው ለሦስት ደቂቃዎች እንዲዘገይ ማድረጋቸው ተጠቅሷል። ለዚህ ተጨማሪ ጥፋት የአራት ጨዋታዎች እገዳና የአምስት ሺህ ብር መቀጮ በመወሰኑ፣ አጠቃላይ ቅጣታቸው ወደ10 ጨዋታዎችና 10 ሺህ ብር ከፍ ብሏል።

መሳይ ተፈሪ ከወላይታ ድቻ ጋር የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፣ በመጀመሪያው የክለቡ ቆይታቸው ቡድኑን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ከማሳደግ ባለፈ፣ በትንሽ በጀት ተወዳዳሪ ቡድን በመገንባት ስማቸውን ያስተዋወቁ አሰልጣኝ ናቸው። የክለቡን የመጀመሪያ የኢትዮጵያ ዋንጫ ድል በማስመዝገብም በቡድኑ ታሪክ ጉልህ አሻራ አስቀምጠዋል።

በክለብ ደረጃ ካካበቱት ልምድ ባሻገር፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በረዳትነትና በዋና አሰልጣኝነት አገልግለዋል። በገብረመድህን ኃይሌ ሥር ረዳት አሰልጣኝ ከነበሩ በኋላ የዋና አሰልጣኝነቱን ኃላፊነት ተረክበው ዋልያዎቹን መርተዋል። አሁን ቡድኑን እየመሩ ያሉት ዮሐንስ ሳህሌ ከመሾማቸው በፊትም በቦታው የነበሩት አሰልጣኝ መሳይ ሲሆኑ፣ ከብሔራዊ ቡድኑ ቆይታቸው በኋላ ወደ ቀድሞ ክለባቸው ወላይታ ድቻ ተመልሰዋል።

በአሰልጣኝነት ዘመናቸው በመልካም ዲሲፕሊን፣ በትሕትናቸውና በእርጋታቸው የሚታወቁት መሳይ፣ በዚህ ጨዋታ ላይ ከተለመደው ባህሪያቸው በተለየ የዲስፒልን ግድፈት እንዲያሳዩ ያደረጋቸው ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተደጋጋሚ የሚታዩ የዳኝነት ስህተቶች ቅሬታ ቢያስነሱም፣ ይህ ዳኞችን ለመሳደብ ወይም ለመማታት ምክንያት ሊሆን አይችልም። እንደ መሳይ ያሉ ልምድ ያላቸው አሰልጣኝ፣ በተለይ በውጥረት ወቅት ስሜታቸውን በመቆጣጠር ለተጫዋቾቻቸው፣ ለአሰልጣኝ ቡድናቸውና ለደጋፊዎች መልካም ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

በተመሳሳይ ጨዋታ የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ሁለተኛውን ረዳት ዳኛ በድንጋይ መምታታቸውን የሚገልጽ ሪፖርት በመቅረቡ፣ ክለቡ 50 ሺህ ብር እንዲከፍልም ተወስኗል።