የኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለፉት ቅርብ ወራቶች ያስመዘገባቸው ዓለም አቀፍ ውጤቶች ከአንድ ቡድን ወይም ከአንድ አሰልጣኝ አቅም በላይ የሆነ ጥያቄ ያስነሳሉ። ከዋናው የወንዶች ብሔራዊ ቡድን እስከ ወጣት ቡድኖች፣ ከሴቶች ብሔራዊ ቡድን እስከ አገሪቱን በአፍሪካ የክለቦች ውድድር የወከሉት ክለቦች ድረስ የታዩት ውጤቶች፣ የእግር ኳሳችን ደረጃ የት እንደሚገኝና ወደየት እያመራ እንደሆነ በጥልቀት እንድንመለከት ያስገድዳል።

በዋናው የወንዶችና የሴቶች ቡድኖች እንዲሁም በተለያዩ የዕድሜ እርከኖችና በክለብ ደረጃ የሚደጋገሙት ከባድ ሽንፈቶች፣ ግብ የማስቆጠር ችግሮችና ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ የሚደረጉ ትግሎች በአጋጣሚ የተፈጠሩ ናቸው ብቻ ብሎ ሊታለፉ አይገባም። ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሱዳንንና ሴኔጋልን በገጠሙባቸው ሁለት ጨዋታዎች በሜዳቸዉም ሆነ ከሜዳቸዉ ዉጭ በተመሳሳይ 1–0 ውጤት ተሸንፈዋል። በሁለቱም ጨዋታዎች አንድም ግብ ሳያስቆጥሩ ሁለት ግቦች ተቆጥረውባቸዋል። በሴኔጋል መሸነፍ ብቻውን የውድቀት መለኪያ ባይሆንም፣ ተከታታይ ጨዋታዎችን ያለ ግብና ያለ ነጥብ ማጠናቀቅ የቡድኑን ተፎካካሪነት ጥያቄ ዉስጥ ያስገባል።

ከ20 ዓመት በታች የወንዶች ብሔራዊ ቡድንም በሴካፋ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሩዋንዳ ጋር 0–0 ከተለያየ በኋላ፣ በታንዛኒያ 4–0 ተሸንፎ ከምድቡ ማለፍ ሳይችል ቀርቶዋል። ቡድኑ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ አቻና አንድ ሽንፈት አስመዝግቦ፣ አንድም ግብ ሳያስቆጥር አራት ግቦች ተቆጥረውበታል። በተመሳሳይ ውድድር ታንዛኒያና ሱዳን ወደ ፍጻሜ ሲደርሱ፣ ኢትዮጵያ ከምድቧ ማለፍ አልቻለችም። ዋናው ብሔራዊ ቡድንና ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ በድምሩ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች አንድም ድል አለማግኘታቸውና አንድም ግብ አለማስቆጠራቸው ልዩ ትኩረት ይፈልጋል። ሦስት ሽንፈቶችና አንድ አቻ በተመዘገቡባቸው በእነዚህ ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ተቆጥረውባቸዋል። ይህ የነጥብ መጥፋት ብቻ ሳይሆን፣ በሁለት የተለያዩ ደረጃዎች የማጥቃት ውጤታማነት ችግር መታየቱን ያመለክታል።

ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ ደግሞ ተስፋና ስጋትን በአንድ ጉዞ አሳይቷል። ቡሩንዲን 3–0 በማሸነፍና ከዩጋንዳ ጋር 1–1 በመለያየት ከምድቡ ማለፉ አበረታች ነበር። ሆኖም በግማሽ ፍጻሜው በዩጋንዳ 4–0፣ ለሦስተኛ ደረጃ በተደረገው ጨዋታም በሩዋንዳ 2–1 ተሸንፎ ለአፍሪካ ዋንጫ ሳያልፍ ቀርቶዋል። ቡድኑ በአጠቃላይ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንዱን አሸንፎ፣ አንዱን አቻ ተለያይቶ፣ በሁለቱ ተሸንፏል፤ አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሰባት ተቆጥረውበታል። በተለይ በመጨረሻዎቹ ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ተቆጥሮበት አንድ ብቻ ማስቆጠሩ፣ በምድብ ደረጃ ያሳየውን አቋም ለምን መቀጠል እንዳልቻለ እንድንመረምር ያደርጋል።

ሉሲዎቹ ከሩዋንዳ ጋር ባደረጓቸው ሁለት የኦሊምፒክ ማጣሪያ ጨዋታዎች አንድ ድልና አንድ አቻ አስመዝግበው፣ ሁለት ግቦችን አስቆጥረው አንድ ብቻ ተቆጥሮባቸዋል። ከሜዳቸው ውጭ 1–0 አሸንፈው፣ በሜዳቸው 1–1 በመለያየት በድምር 2–1 ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል። ሉሲዎቹ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸው እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ስኬት ነው። ይሁንና በሜዳቸው አቻ ተለያይተው በአንድ ግብ የድምር ብልጫ ማለፋቸው፣ በቀጣይ ዙሮች ለሚጠብቋቸው ፈተናዎች ያላቸውን ዝግጁነት መገምገም አስፈላጊ ነው።

በክለቦች ደረጃ የታየው ምስል ደግሞ የበለጠ አሳሳቢ ነው። ሲዳማ ቡና በመጀመሪያው ዙር ከአይግሎንስ ጋር ከሜዳው ውጭ 0–0 ተለያይቶ፣ በመልሱ 3–0 በማሸነፍ አልፎ ነበር። በቀጣዩ ዙር ግን በሱዳኑ አል ሂላል በሁለቱም ጨዋታዎች 2–0 ተሸንፎ፣ በድምር 4–0 ከቻምፒዮንስ ሊጉ ተሰናብቷል። ሲዳማ በአጠቃላይ ባደረጋቸው አራት የካፍ ጨዋታዎች አንድ ድል፣ አንድ አቻና ሁለት ሽንፈቶች አስመዝግቦ፣ ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ አራት ተቆጥረውበታል።

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲም በመጀመሪያው ዙር በአል ሂላል አል ሳህል 2–1 ከተሸነፈ በኋላ፣ በመልሱ በተመሳሳይ 2–1 ውጤት አሸንፎ፣ በመለያ ምቶች 4–1 ወደ ቀጣዩ ዙር ተሸጋግሮ ነበር። ሆኖም በሊቢያው አል አህሊ ትሪፖሊ በሜዳው 4–0፣ በመልሱም 4–1 ተሸንፎ በድምር 8–1 ከኮንፌዴሬሽን ካፑ ወጥቷል። በአራቱ ጨዋታዎች አንድ ድልና ሦስት ሽንፈቶች ያስመዘገበው ወልዋሎ፣ አራት ግቦችን ሲያስቆጥር 11 ተቆጥረውበታል። ይህ የግብ ድምር የመለያ ምቶችን አያካትትም። የኢትዮጲያ ክለቦች የማጣሪ ማጣሪያ ላይ የሚያገኙዋቸዉን ደካማ ቡድኖች ማሸንፍ ቢችሉም፣ ባብዛኛው በሚቀጥለው ዙር ክተሻለ ሊግ የሚመጡ ቡድኖች በሰፋ ጎል ሲሸነፉ ማየት የተለመደ ክስተት ሆኖዋል።

ሁለቱ ተወካይ ክለቦች በድምሩ ካደረጓቸው ስምንት ጨዋታዎች ሁለቱን ብቻ አሸንፈው፣ አንዱን አቻ ተለያይተው፣ በአምስቱ ተሸንፈዋል። ሰባት ግቦችን ሲያስቆጥሩ 15 ተቆጥረውባቸዋል። በተለይ በሁለተኛው ዙር አራቱንም ጨዋታዎች ተሸንፈው፣ 12 ግቦችን አስተናግደውና አንድ ብቻ አስቆጥረው መሰናበታቸው፣ ከጠንካራ አህጉራዊ ተጋጣሚዎች ጋር ያለውን ልዩነት በግልጽ ያሳያል።

እነዚህን ውጤቶች አንድ ላይ ስንመለከት፣ ችግሩን በአንድ ተከላካይ ስህተት፣ በአንድ አሰልጣኝ ምርጫ ወይም በአንድ ጨዋታ እድለቢስነት ነው በሎ ማስረዳት ይከብዳል። ዋናው ብሔራዊ ቡድን ግብ ማስቆጠር ሲቸገር፣ ወጣት ቡድኖች በክፍለ አሁጉራዊ ተጋጣሚዎች በሰፊ ልዩነት ሲሸነፉ፣ ተወካይ ክለቦችም ከምድብ ደረጃው በፊት በከባድ ውጤት ሲወጡ፣ የጋራ መሠረታዊ ችግር መኖሩን የሚያሳይ በቂ ምክንያት ነው። ያንን ችግር በትክክል መለየት ግን ገለልተኛ ጥናት ይፈልጋል።

ከዚህ ይበልጥ የሚያሳስበው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ታላላቅ ቡድኖች ጋር ያላት ርቀት ብቻ አይደለም። በምሥራቅና በመካከለኛው አፍሪካ ካሉ አገራትም ጋር መፎካከር እየከበደ መምጣቱን ነው። የሶማሊያ የወጣቶች እግር ኳስ እድገትም በዚህ ረገድ ግልጽ ምሳሌ ነው። ሶማሊያ በዘንድሮው የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ውድድር እስከ ፍጻሜ ደርሳ፣ ከዩጋንዳና ከሩዋንዳ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋን አረጋግጣለች። ኢትዮጵያ ግን ከእነዚህ ሦስት ቦታዎች አንዱን ማግኘት አልቻለችም። ይህ የሶማሊያን ስኬት በአድናቆት እያየን፣ የራሳችንን የተጫዋች እደገተና የውድድር ዝግጅት እንድንፈትሽ የሚያስገድድ ነው።

በሴቶች እግር ኳስም ኬንያ ወጣት ተጫዋቾቿን ከዕድሜ እርከን ውድድሮች ወደ ዋናው ብሔራዊ ቡድን የማሸጋገር ሂደት እያሳየች ነው። በ2024 የከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ የተሳተፉ ተጫዋቾቿ ለዋናው ቡድን አስተዋጽኦ ማድረግ ጀምረዋል። እንደ ምዋናሊማ አዳም ጀሬኮ ያሉ ተጫዋቾች ደግሞ ከቱርክ ሊግ ወደ አሜሪካው ካንሳስ ሲቲ ከረንት የመሸጋገር ዕድል አግኝተዋል። እነዚህ ምሳሌዎች የወጣቶች ውድድር፣ የብሔራዊ ቡድን እድገትና የውጭ ዕድል እንዴት ሊያያዙ እንደሚችሉ ያሳያሉ። ይህ ማለት የክልሉ አገራት ሁሉንም ችግሮቻቸውን ፈትተዋል ማለት አይደለም። ለኢትዮጵያ ግን ዋናው ጉዳይ፣ በተለያዩ የድሜ እርክን ላይ የሚታየውን ብልጭታ ማስቀጠል አልመቻል ነው።

በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከዕለታዊ አስተዳደሩና ከውስጥ ግንኙነቶች ነፃ በሆኑ ባለሙያዎች አጠቃላይ ጥናት ማስደረግ አለበት። ጥናቱ የተጫዋች ልማትን፣ የወጣቶች ውድድር ቀጣይነትን፣ የአሰልጣኞች ትምህርትንና ምርጫን፣ የክለቦች አካዳሚዎችን፣ የሴቶች እግር ኳስ ድጋፍንና የብሔራዊ ቡድኖች ዝግጅትን በአንድ ላይ መመርመር ይገባዋል። በተለይ ወጣት ተጫዋቾች በዓመት ውስጥ ስንት ጨዋታዎችን እንደሚያደርጉ፣ ከአንድ የዕድሜ እርከን ወደ ሌላው እንዴት እንደሚሸጋገሩና በክለቦቻቸው ምን ያህል የመጫወት ዕድል እንደሚያገኙ መለካት ያስፈልጋል። ለአንድ አጭር ማጣሪያ ተሰብስቦ የሚበተን ቡድን፣ ዓመቱን ሙሉ በተደራጀ ውድድርና ሥልጠና ከሚያሳልፍ ተጋጣሚ ጋር እኩል እንዲወዳደር መጠበቅ አይቻልም።

የጥናቱ ውጤት ለሕዝብ ቀርቦ፣ የተለዩትን ችግሮች የሚመልስ የተግባር ዕቅድ ሊዘጋጅ ይገባል። ዕቅዱ ግልጽ በጀት፣ የአፈጻጸም ጊዜ፣ ተጠያቂ አካላትና የእድገት መለኪያዎች ሊኖሩት ይገባል። የፌዴሬሽኑ ሥራ የሚመዘነው ቡድኖችን ወደ ውድድር በመላክ ብቻ ሳይሆን፣ እነዚያ ቡድኖች ከቀድሞው ምን እንዳሻሻሉ፣ ስንት ተጫዋቾችን ወደ ቀጣይ ደረጃ እንዳሸጋገሩና በሜዳ ላይ ምን ያህል ተወዳዳሪ እንደሆኑ በመገምገም መሆን አለበት።