ዳንኤል ፀሐዬ በምን መስፈርት ተመረጡ? የብሔራዊ ቡድኑ ስብስብስ የወደፊቱን ትውልድ ለመገንባት የተዘጋጀ ነው?

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዳንኤል ፀሐዬን የከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ መምረጡና በቅርቡ የተደረገው የተጫዋቾች ጥሪ በእግር ኳስ ተከታታዮች ዘንድ ጥያቄ አስነስቷል። በተለይም የአሰልጣኙ የቅርብ ዓመታት የክለብ ውጤትና በስብስቡ የተካተቱ ተጫዋቾች ምርጫ የፌዴሬሽኑን የአሰልጣኞች ሹመት መስፈርት እንድንመለከት ያስገድዳል።

የዳንኤል ፀሐዬ ሹመት፤ ብቃት ወይስ ሌላ መስፈርት?

አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ በቅርብ ዓመታት በክለብ ደረጃ ያስመዘገቡት ውጤት ለዚህ ኃላፊነት መመረጣቸውን አጠያያቂ ያደርገዋል። ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት የመሯቸው ሁለት የተለያዩ ክለቦች ከሊጉ መውረዳቸውና ዝቅተኛ የማሸነፍ ቁጥር ማስመዝገባቸው በሹመቱ ወቅት ግምት ውስጥ ሊገባ የሚገባ የሥራ ታሪክ ነው። እርግጥ ነው፣ አንድ ክለብ ከሊግ መውረዱ የአሰልጣኙ ብቻ ኃላፊነት አይደለም። የክለቡ የፋይናንስ አቅም፣ የተጫዋቾች ጥራትና የአመራር ሁኔታ በውጤት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ሆኖም በተከታታይ ዓመታት የታየ ደካማ አፈጻጸም የአሰልጣኝን ብቃት ለመገምገም ከሚያገለግሉ ዋና መለኪያዎች አንዱ ነው።

በአንጻሩ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ በሥራቸው የተሻለ ውጤት ያሳዩ አሰልጣኞች አሉ። እንደነሙሉጌታ ምህረትና፣ ከአንድ የውድድር ዘመን በፊት የሊጉን ዋንጫን ያነሱት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሰልጣኝ በጸሎት ልኡልሰገድ፣ እንዲሁም በነገሌ አርሲ ከተማ እያሳዩት ባለው ውጤት ትኩረት የሳቡት ቱሉ ደስታ ለዚህ ምሳሌ የሚሆኑ ወጣት አሰልጣኞች ናቸው። እነዚህን የመሳሰሉ አሰልጣኞች በብሔራዊ ቡድን ኃላፊነት ለመሥራት ዕድል ሊሰጣቸው ወይም ቢያንስ በእጩነት ሊታዩ ይገባ ነበር። ይህ ማለት ግን ከተጠቀሱት አሰልጣኞች አንዱ የግድ መሾም ነበረበት ማለት ሳይሆን፣ የተሻለ ውጤት ያሳዩ አሰልጣኞች እያሉ ዳንኤል ፀሐዬ በምን መስፈርት ቅድሚያ እንዳገኙ ለመጠየቅ ነው።

የቀድሞው የብሔራዊ ቡድን ሹመት

ዳንኤል ፀሐዬ በቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ዘመን ረዳት አሰልጣኝ ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል። በወቅቱ በእግር ኳስ አመራር ውስጥ የፖለቲካ ተጽዕኖና የግል ትውውቅ በሹመቶች ላይ ሚና እንዳላቸው ትችቶች ይነሱ ነበር። ይሁን እንጂ የዳንኤል ሹመት በፖለቲካዊ ትስስር የተፈጸመ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሳይኖር እንደ እውነታ መቅረብ አይገባውም። ሆኖም በወቅቱ ከእሳቸው የበለጠ የስልጠና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እያሉ ለዚያ ኃላፊነት መመረጣቸው አጠያያቂ ነበር። አሁንም በክለብ ደረጃ የተሻለ ውጤት ያሳዩ አሰልጣኞች እያሉ ሌላ የብሔራዊ ቡድን ኃላፊነት ማግኘታቸው ግልጽ ማብራሪያ የሚፈልግ ጉዳይ ነው።

የተጫዋቾች ምርጫ፤ የተለመዱ ስሞችና የታዳጊዎች ዕድል

ከአሰልጣኙ ሹመት ባሻገር የተጫዋቾች ምርጫም የሚያነጋግር ነው። በስብስቡ ውስጥ ለዓመታት በፕሪሚየር ሊጉ የተጫወቱ፣ ለዋናው ብሔራዊ ቡድንም በተደጋጋሚ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች መካተታቸው የወጣት ብሔራዊ ቡድኑን የልማት ዓላማ ያጠያይቃል። አንድ ተጫዋች ለዓመታት በሊጉ መጫወቱ ብቻ ዕድሜው ከ23 ዓመት በላይ መሆኑን አያረጋግጥም። ሆኖም የዕድሜ ሰነዶች ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ በሚነሳበት የእግር ኳስ ሥርዓት ውስጥ ፌዴሬሽኑ የውድድሩን የዕድሜ መስፈርት በጥንቃቄ ማረጋገጥ አለበት። ከዚያም በላይ በፓስፖርት እድሜ መለኪያ ብቻ ሳይሆን የተጫዋቹ የወደፊት እድገት በምርጫው ውስጥ ትልቅ ቦታ ሊኖረው ይገባል። በዚህ ሁሉ ትችት መካከል በአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ምርጫ ውስጥ አዎንታዊ ጎኑ፣ ሶስት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በከ23 ዓመት በታች ስብስብ ዉስጥ መካተታቸው ሊደነቅ የሚገባው ውሳኔ ነው። ዳንኤል ለዚህ ምርጫ እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል። ነገር ግን በሊጉ እየታዩ ካሉ በርካታ ተስፋ ሰጪ ታዳጊዎች አንጻር የሶስቱ ተጫዋቾች መካተት ብቻ በቂ አይደለም።

በፕሪሚየር ሊጉ የታዩ ተስፋ ሰጪ ወጣቶች ለምን ተዘነጉ?

በቅርብ ዓመታት ሀዲያ ሆሳዕና፣ ሀዋሳ ከተማና ወላይታ ዲቻ ከወጣት ቡድኖቻቸው ያሳደጓቸው ተጫዋቾች በፕሪሚየር ሊጉ ብቃታቸውን እያሳዩ ቢሆንም በዚህ ስብስብ አለመካተታቸው ያስገርማል። በተለይ ሀዲያ ሆሳዕና ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ በርካታ ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን በማሳደግ በሊጉ የመጫወት ዕድል ሰጥቷቸዋል። ከእነዚህ መካከል ታሪኩ ፀደቀና ሱራፌል ተመስገን ባለፈው የውድድር አመት በብቃታቸው ትኩረት ከሳቡ ወጣቶች መካከል ይጠቀሳሉ። ሁለቱ ተጫዋቾች ገና በከ20 ዓመት በታች የዕድሜ ክልል ውስጥ ሆነው በሊጉ የመሰለፍ ዕድል አግኝተዋል። በተመሳሳይ ከወጣት ቡድኑ ያደገው የግራ ተከላካዩ ናትናኤልም በሀዲያ ሆሳዕና ዋና ቡድን ውስጥ ጉልህ ሚና ተጫውቷል። በዚህ ዝርዝር ውስጥ የሀዲያ ሆሳዕናውን ወጣት ግብ ጠባቂና በከ20 ዓመት በታች ውድድር ጥሩ ብቃት ያሳየውን የኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂም ሊካተቱ ይገባ ነበር።

እነዚህን ስሞች እንደምሳሌ አነሳን እንጂ በሊጉ በተለያዩ ክለቦች ውስጥ የመጫወት ዕድል እያገኙ ያሉ ታዳጊዎች በተገቢው ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን መጠራት አለባቸው። ዕድሜያቸው ወደ 20ዎቹ መጨረሻ ከደረሰ በኋላ እንደ አዲስ ተስፋ ሰጪ ተጫዋቾች የሚታዩበት አሰራር ሊቆም ይገባል። የአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ሹመትና የተጫዋቾች ምርጫ ያስነሱት ጥያቄ ከአንድ ግለሰብ በላይ የሆነ፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ለብቃትና ለወጣቶች ልማት ምን ያህል ቅድሚያ እየተሰጠ እንደሆነ የሚያመለክት ጉዳይ ነው። ፌዴሬሽኑም አሰልጣኞችን ሲሾም የሚከተለውን መስፈርት ግልጽ ማድረግ፣ በውጤትና በብቃት የተለዩ አሰልጣኞችን በፍትሐዊነት ማወዳደርና ለወጣቶች እድገት የተቀናጀ አሠራር መዘርጋት ይጠበቅበታል።

የወጣት ብሔራዊ ቡድን ስኬት የሚለካው በዛሬው የጨዋታ ውጤት ብቻ ሳይሆን፣ ለነገው ዋና ብሔራዊ ቡድን ስንት ብቁ ተጫዋቾችን ማዘጋጀት እንደቻለ ጭምር ነው።