የ2019 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሦስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ በአራት ጨዋታዎች ሲጠናቀቅ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ የሊጉን 3 ነጥብ ፍለጋው እስካሁን አልተሳካም። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሀዋሳ ባገኘው አንድ ነጥብ የሰንጠረዡን መሪነት ሲያስጠብቅ፣ ባህር ዳር ከተማና መቻል ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ፦ የመጀመሪያ ድል ፍለጋና የደጋፊዎች ትዕግሥት
በአሰልጣኝ ሚቾ እየተገነባ የሚገኘው አዲሱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስብስብ፣ በሦስተኛው የሊግ ጨዋታውም ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት አልቻለም። በአዲስ አበባ ስታዲየም ከአዳማ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ፣ ቀድሞ ግብ ተቆጥሮበት ከኋላ በመነሣት 1–1 ተለያይቷል። አዳማ ከተማ በ10ኛው ደቂቃ ቢንያም አይተን ባስቆጠረው ግብ መሪነቱን ይዟል። ሆኖም ግቡ ከጨዋታ ውጭ ከሚመስል አቋቋም በተነሣ እንቅስቃሴ መገኘቱ አከራካሪ ነበር። ጊዮርጊስ አቻ ለመሆን ሲታገል ቆይቶ፣ በ63ኛው ደቂቃ አብዱልሀሚድ ሙባረክ ባስቆጠረው የጭንቅላት ግብ ወደ ጨዋታው ተመልሷል። የአቻነት ግቡ የተገኘበት የማዕዘን ምት ውሳኔም እንዲሁ ጥያቄ የተነሣበት ነበር። የዋና ዳኛውና በተለይ የረዳት ዳኞቹ ውሳኔዎች በጨዋታው ሂደት ላይ ጥላ አጥልተዋል። በሁለቱም ግቦች አመጣጥ የታዩት የተሳሳቱ ውሳኔዎች፣ ሁለቱንም ቡድኖች በተለያየ ጊዜ ተጠቃሚ አድርጎዋል።
ከዳኝነቱ ባሻገር ግን ጊዮርጊስ ራሱን መጠየቅ ያለበት ጥያቄ አለ። አዲስ አሰልጣኝ ሐሳቡን ለመተግበርና አዲስ ስብስብ ለማዋሃድ ጊዜ መፈለጉ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ደጋፊዎች በትዕግሥት እንዲጠብቁ፣ በሜዳ ላይ የሚታይ እድገትና ተስፋ ሰጪ አጨዋወት ከቡዱኑ እየታየ አለመሆኑ፣ ይህ ትግስት ለምን ያህል ጊዜ ይዘልቃል የሚለው አጠያያቂ ጉዳይ ነው። የዛሬውም ጨዋታ ከቀደመው ጨዋታ ብዙም መሻሻል አላሳየም። ውጤቱ እየዘገየ፣ አጨዋወቱም ደጋፊዎችን የሚያረካ መልክ ሳይይዝ ሲቀጥል፣ ለሚቾና ለአዲሱ ቡድናቸው የሚሰጠው የትዕግሥት ጊዜ እስከ መቼ ይዘልቃል የሚለዉን አብረን እናያለን?
ባንክ ከሜዳው ዉጭ ነጥብ ተጋርቶ፤ የሊግ መሪነቱንም አስጠበቀ
ሀዋሳ ከተማና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1–1 ተለያይተዋል። ባለሜዳው ቡድን በ5ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠረው ግብ ቀድሞ መሪ ቢሆንም፣ ያንን ብልጫ እስከ መጨረሻው ማስጠበቅ አልቻለም። ባንክ በ84ኛው ደቂቃ ሎዌ ሎኛ ባስቆጠረው ደንቅ የጭንቅላት የአቻነት ግብ ከሽንፈት አምልጧል። ሁለቱ ቡድኖች በተለያዩ አጋማሾች ባስቆጠሯቸው ግቦች ነጥብ ተጋርተዋል፣ ባንክ ከሜዳው ውጭ 1 ነጥብ ያገኘበት ውሎ ሆኗል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዚህ ውጤት ያለመሸነፍ ጉዞውን አስቀጥሎ፣ በሁለት ድሎችና በአንድ አቻ ሰባት ነጥብ በመሰብሰብ በሰንጠረዡ አናት ተቀምጦዋል።
አንተነህ ተፈራ በሁልት ግብ ባህር ዳርን አሸናፊ አርጎዋል
በሀላባ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ባህር ዳር ከተማ ወላይታ ድቻን 3–1 በማሸነፍ ከባለፈው ሳምንት ሽንፈት አገግሟል። ጨዋታውም በዘንድሮው ሊግ በአንድ ጨዋታ አራት ግቦች የተቆጠሩበት የመጀመሪያው ሆኗል። የባህር ዳርን የሸናፊነት መንገድ የከፈተው አንተነህ ተፈራ፣ በ15ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል። አጥቂው በ55ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን በመጨመር፣ በዚህ የውድድር ዓመት በአንድ ጨዋታ ሁለት ግብ ያስቆጠረ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል። ወላይታ ድቻ በ64ኛው ደቂቃ መልካሙ ቦጋለ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠረው ግብ ልዩነቱን አጥብቦ ወደ ጨዋታው የመመለስ ተስፋ አግኝቶ ነበር። ሆኖም በ90+5ኛው ደቂቃ ብሩክ ሰሙ ለባህር ዳር ሦስተኛውን ግብ በማስቆጠር የተጋጣሚውን ተስፋ አጨልሞ፣ የቡድኑን ሦስት ነጥብ አረጋግጧል።
መቻል አሸነፈ፤ ጋሞ ጨንቻ የመጀመሪያ ነጥቡን ፍለጋ ቀጥሏል
በአርባ ምንጭ አባያ ካምፓስ ስታዲየም መቻል፣ ቲቶ ኦኬሎ በ44ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ጋሞ ጨንቻን 1–0 አሸንፏል። ውጤቱ መቻልን ወደ ድል ሲመልስ፣ አዲስ አዳጊው ባለሜዳ የመጀመሪያ ነጥቡን ፍለጋ እንዲቀጥል አድርጎታል። ለጋሞ ጨንቻ በሊጉ መቆየት የሚጠይቀው ፈተና ገና ከጅምሩ እየከበደ ነው። አዲስ አዳጊ ቡድኖች ከሊጉ ጋር ለመላመድ ጊዜ ቢፈልጉም፣ በተለይ በራስ ሜዳ ነጥብ መሰብሰብ ወሳኝ ነው። ቡድኑ በጊዜ ነጥቦችን ማስመዝገብ ካልጀመረ፣ በቀጣዩ የሊጉ ረጅም ጉዞ ላይ ጫናውን ሊያበዛበት ይችላል። የደጋፊዎች ተሳትፎም ከተጠበቀው በታች ነበር። የሜዳ ጨዋታው በብዙ ደጋፊዎች ታጅቦ ይደምቃል ተብሎ ቢጠበቅም፣ በስታዲየሙ የታዩት ባዶ መቀመጫዎችና የተቀዛቀዘው ድባብ ለባለሜዳው የሚጠበቀውን ድጋፍ አለምግኘቱ በአሉታ ሊነሳ የሚችል ጉዳይ ነው።
በኳስ ቁጥጥርና በቅብብል ላይ በተመሠረተ አጨዋወት የሚታወቁት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ፣ ዛሬ ቡድናቸው ያንን ፍሰት ሲያሳይ አልታየም። እንቅስቃሴው የተቆራረጠና በተጫዋቾች መካከል ያለው ቅንጅት የላላ ነበር። የሜዳው ጥራት ለዚህ አጨዋወት አንዱ እንቅፋት ሊሆን ይችላል። ኳስን በመሬት በማንቀሳቀስ ለመጫወት ለሚፈልግ ቡድን፣ ተስማሚ ያልሆነ ሜዳ የቅብብል ፍሰትን ያውካል። የመጫወቻ ሜዳዎች ሁኔታ በየሳምንቱ መነጋገሪያ እየሆነ መቀጠሉም ትኩረት ይፈልጋል።
ሦስተኛው ሳምንት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሰባት ነጥብ የሰንጠረዡ መሪ ሆኖ ቀጥሏል። የአራተኛው ሳምንት መርሐ ግብር ቅዳሜ ሀዲያ ሆሳዕናንና ፋሲል ከነማን በሚያገናኝ አንድ ጨዋታ ይጀምራል
