ክፍል አንድ
የ2019 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መስከረም 29 ቀን 2019 ዓ.ም ይጀመራል። ባለፈው የውድድር ዘመን 20 ክለቦችን በሁለት ምድቦች በመክፈል የተካሄደው ሊግ፣ ዘንድሮ 18 ክለቦች በሜዳቸውና ከሜዳቸው ውጪ (Home and Away) እርስ በርስ ሁለት ጊዜ የሚገናኙበትን የውድድር አወቃቀር ይዞ ይመለሳል። ይህም እያንዳንዱ ክለብ 17 ጨዋታዎችን በሜዳው፣ 17 ጨዋታዎችን ከሜዳው ውጪ በድምሩ 34 የሊግ ጨዋታዎችን እንዲያደርግ ያደርጋል።
የዋንጫ ፉክክሩ እና ከወራጅ ቀጠና ለማምለጥ የሚደረገው ትግል የዘንድሮውን ውድድር እጅግ ተጠባቂ ያደርጉታል።
ሲዳማ ቡና ሻምፒዮንነቱን ማስጠበቅ ቀዳሚ አላማው ሲሆን፣ ነገሌ አርሲ በበኩሉ የባለፈው ዓመት ደረጃው የአንድ ዓመት ክስተት እንዳልነበር ለማሳየት ይፋለማል። መቻል በውበቱ አባተ አሰልጣኝነት ከፍ ማለትን ያልማል፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በሚቾ ስሬዶዬቪች መሪነት ወደ ለመደው የዋንጫ ፉክክር ለመመለስ አዲስ ፕሮጀክት ጀምሯል።
Football Ethiopia የ18ቱን ክለቦች፣ የተጫዋቾቻቸውን አቅም፣ የአሰልጣኞቻቸውን ተፅዕኖ እና በአዲሱ የውድድር ዓመት ይዘው የሚመጡትን ጠንካራና ደካማ ጎኖች በሁለት ክፍሎች ይመለከታል።
1. ሲዳማ ቡና | ዋንጫውን ማስጠበቅ የሚችል ስብስብ?
ሲዳማ ቡና ወደ አዲሱን ዓመት የሚጀምረው ሁሉም ቡድን እንዲኖረው በሚፈልገው ነገር "ዋንጫ" እጁ ላይ ይዞ ነው። ባለፈው ዓመት ከ38 ጨዋታዎች 68 ነጥብ ሰብስቦ ሻምፒዮን ሲሆን 43 ግቦችን አስቆጥሮ 23 ጎል ብቻ አስተናግዷል። ይህ ቁጥር ሻምፒዮንነቱ በማጥቃት ላይ ብቻ ሳይሆን በሚዛናዊ የቡድን አቀራረብ ላይ የተገነባ መሆኑን ያሳያል።
መስፍን ታፈሰ፣ አቤል ያለው፣ ብርሃኑ በቀለ፣ ያሬድ ባዬ እና ደግፌ ዓለሙን የመሳሰሉ ወሳኝ ተጫዋቾች ከቡዱኑ ጋር መቆየታቸው የስብስቡን ጥራት ያሳድጋል። አንድነቱንና የመከላከል ሚዛኑን ማስቀጠል ከቻለ ዋንጫውን ለማስጠበቅ የሚያስችል መሠረት አለው።
ዋነኛው ፈተና ግን የአለፍውን አመት ስኬት መድገም ነው። ከዚህ በተጨማሪ የአፍሪካ ውድድርና ሊጉን በአንድ ጊዜ ማስኬድ በተጫዋቾች አካላዊ ብቃትና በስብስቡ ጥልቀት ላይ ተጨማሪ ጫና ያመጣል።
ጠንካራ ጎን፦ የተረጋጋ ስብስብ፣ የመከላከል ጥንካሬ፣ የሻምፒዮንነት ልምድ።
ትልቁ ፈተና፦ ሻምፒዮንነቱን መድገምና የሊግ/አፍሪካ ውድድሮችን በሚዛናዊነት ማስኬድ።
2. ቅዱስ ጊዮርጊስ | በሚቾ የሚገነባው አዲሱ ቡድን
ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ያለው ታሪክ ራሱ ክለቡ ሁልጊዜ ዋንጫ እንዲጠበቅ ያደርገዋል። የቅርብ ዓመታት ውጤት ግን ከዚህ በተቃራኒ ነበር።
ዘንድሮ ሚሉቲን “ሚቾ” ስሬዶዬቪች ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ክለቡ ተመልሰው ዋና አሰልጣኝ ሲሆኑ፣ ስዩም ከበደ የቴክኒክ ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል። ክለቡ የወጣት ተጫዋቾችን ድርሻ በማሳደግ አዲስ ቡድን ለመገንባት መምረጡ የሚቾን ስራ የበለጠ ፈታኝ ያደርገዋል።
ተመስገን ብረሃኑ፣ ሀብታሙ ጉልላት፣ ጸጋአብ ግዛዉና ሌሎች ወጣት ተጫዋቾች የአዲሱ ፕሮጀክት አካል ሲሆኑ፣ የሚቾ የአፍሪካ እግር ኳስ ልምድ ለዚህ ቡድን ትልቅ እሴት ሊሆን ይችላል።
ፈተናው ግን የጊዜ ጉዳይ ነው። ብዙ ለውጥ ያደረገ ስብስብ አንድ ወጥ የጨዋታ ማንነት ለመፍጠር ጊዜ ይፈልጋል፤ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የውጤት ጥማት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይሆንም።
ጠንካራ ጎን፦ ልምድ ያለው የቴክኒክ ቡድን፣ ወጣት ተጫዋቾች፣ የክለቡ የውድድር ባህል።
ትልቁ ፈተና፦ አዲሱን ስብስብ በፍጥነት ማዋሃድ።
3. ነገሌ አርሲ | ያለፈውን ስኬት ማረጋገጥ
ነገሌ አርሲ የባለፈው ዓመት ትልቁ ክስተት የሆነ ቡድን ነበር። 38 ጨዋታዎች 60 ነጥብ ሰብስቦ ሁለተኛ በመውጣቱ በሊጉ ውስጥ ተፎካካሪ ቡድን መገንባቱን አሳይቷል።
ሮሆቦት ሰለሎ እና ዳዊት ተፈራን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ለቡድኑ ጥራት ይሰጡታል። ትልቁ ጥያቄ ግን ነገሌ አርሲ አሁን በተጋጣሚዎች በበለጠ ትኩረትና እይታ ዉስጥ ሆኖ ተመሳሳይ ውጤት ማምጣት ይችል ይሆን? የሚለው ነው።
ጠንካራ ጎን፦ የቡድን አንድነት፣ የተረጋጋ አደረጃጀት፣ የራስ መተማመን።
ትልቁ ፈተና፦ ያለፈውን ዓመት ዉጤታማነት ማስቀጠል።
4. መቻል | የተጨዋቾች ጥራት፤ የሚፈለገው ዋንጫ?
በ44 ግቦች እና በ57 ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃ — የመቻል ያለፈው ዓመት ቁጥሮች ቡድኑ በከፍተኛው ደረጃ ለመወዳደር የሚያስችል መሠረት እንዳለው ያሳያሉ።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ያላቸው ልምድ ከግሩም ሀጎስ፣ አማኑኤል ተርፉ፣ ቸርነት ጉግሳና ሌሎች ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች ጋር ሲጣመር መቻልን በሊጉ ውስጥ ከሚጠበቁት ቡድኖች አንዱ ያደርገዋል።
ጠንካራ ጎን፦ ጥልቅ ስብስብ፣ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች፣ ልምድ ያለው አሰልጣኝ።
ትልቁ ፈተና፦ ይህን ስብስብ አዋህዶ ወደ ዋንጫ መቀየር።
5. ፋሲል ከነማ | ጠንካራ የመከላከል አደርጃጀት፤ ግብ የማስቆጠር ችግር?
ፋሲል ከነማ በመከላከል ላይ ያለው ዲሲፕሊን ዋነኛ መለያው ነው። ባለፈው ዓመት 28 ግቦች ብቻ ተቆጥረውበታል፤ በተቃራኒው ግን 28 ግብ ብቻ ማስቆጠሩ የማጥቃት ምርታማነቱን ጥያቄ ውስጥ ያስገባል።
ጠንካራ ጎን፦ የመከላከል ዲሲፕሊንና ጨዋታን የመቆጣጠር ችሎታ።
ትልቁ ፈተና፦ ግብ የማስቆጠር ችግር።
6. ኢትዮጵያ ቡና | የቡድን ጥራቱን ወደ ዉጤታማነት መቀየር
ኢትዮጵያ ቡና በተለያዩ መስመሮች ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች ለዚህ የውድድር አመት አስፈርሞዋል። አዲሱ ዉጤታማው አሰልጣኝ ገብረምድህን ሃይሌ ቡዱኑን የሚመሩ ሲሆን፤ አቡበከር ኑራ፣ ሀብታሙ ተከስተ፣ ራምኬል ጀምስ እና አብዱሰላም የሱፍ የቡድኑን አማራጮች ያሰፋሉ። በተጨማሪም የቡዱኑ ታማኝ ደጋፊዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ 12ኛ ተጫዋች ሆነው የሚቀጥሉ ይሆናል
ጠንካራ ጎን፦ የተጫዋቾች ጥራት፣ የጥቃት አማራጮች፣ ትልቅ የደጋፊ መሠረት።
ትልቁ ፈተና፦ የቡድን ውህደትና የመከላከል ሚዛን።
7. ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ | ግብ ማስቆጠር የሚችል፣ ሚዛን የሚፈልግ ቡድን
ቡዱኑ ያስቆጠራቸው 45 ግቦች የንግድ ባንክን የማጥቃት አቅም ሲያሳይ፣ 45 ግቦች ማስተናገዱ የቡድኑን ዋነኛ የመከላከል ክፍተት ያሳያል። የማጥቃት አቅሙን ሳያጣ መከላከሉን ማሻሻል ከቻለ በደረጃ ወደ ላይ ከፍ ማለት ይችላል።
ጠንካራ ጎን፦ የማጥቃት አቅምና የግብ አማራጮች።
ትልቁ ፈተና፦ የመከላከል ሚዛን።
8. ባህር ዳር ከተማ | የአቻነት ዉጤቶችን ወደ ሦስት ነጥብ መቀየር
ባህር ዳር ከተማ ባለፈው ዓመት ከ38 ጨዋታዎች 21 ጊዜ አቻ ተለያይቷል። ቡድኑን ለማሸነፍ አስቸጋሪ ቢሆንም ወደ ላይ ለመውጣት ከእነዚህ አቻዎች ጥቂቶቹን ወደ ድል መቀየር ይኖርበታል።
ጠንካራ ጎን፦ የተደራጀ መከላከልና ጨዋታ ውስጥ የመቆየት ችሎታ።
ትልቁ ፈተና፦ ጨዋታዎችን በድል መዝጋት።
9. ወላይታ ድቻ | ለማንም ቀላል ያልሆነ ተጋጣሚ
ወላይታ ድቻ በጠንካራ የቡድን መንፈስ፣ በአካላዊ ፉክክርና በቀላሉ እጅ ባለመስጠት ይታወቃል። 18 አቻዎች የተመዘገቡበት ያለፈው ዓመት ግን እነዚያን ጨዋታዎች ወደ ድል መቀየር ዋነኛው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ያሳያል።
ጠንካራ ጎን፦ የቡድን መንፈስ፣ የሊጉ ልምድ፣ ተወዳዳሪነት።
ትልቁ ፈተና፦ አቻዎችን ወደ ድል መቀየር።
ይቀጥላል — በክፍል ሁለት ቀሪዎቹን 9 ክለቦች እንመለከታለን።
