በ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ምድብ ‘J’ የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ ሴኔጋልን ለመግጠም ዝግጅቱን አጠናቋል። ዋሊያዎቹ ጨዋታውን ነገ 12፡00 ሰዓት በባህር ዳር ስታዲየም ያደርጋሉ።

የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በቅድመ ጨዋታ ጋዜጣዊ መግለጫቸው፣ ቡድኑ ለሴኔጋል ጨዋታ ያደረገውን ዝግጅት ማጠናቀቁን እና ተጫዋቾቹ ለፍልሚያው ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መስፍን ታፈሰ በሁለት ቢጫ ካርዶች ምክንያት ከጨዋታው ውጪ ሲሆን፣ በረከት ወልዴም በጉዳት አይሰለፍም። ከሁለቱ ተጫዋቾች ውጪ ያሉት 21 የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ለጨዋታው ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ናቸው።

አሰልጣኝ ዮሐንስ የባህር ዳር ስታዲየም የጨዋታ ሜዳንም አድንቀው፣ በኢትዮጵያ ካዩዋቸው ምርጥ ሜዳዎች አንዱ መሆኑንና ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ እግር ኳስ ለማሳየት ምቹ ሁኔታ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

ብሔራዊ ቡድኑ በሱዳን ጨዋታ የፈጠራቸውን የግብ ዕድሎች ወደ ግብ አለመቀየሩ ከታዩበት ድክመቶች አንዱ ነበር። አሰልጣኙ ቡድኑ በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን ገልጸው፣ አጥቂዎቹ በሴኔጋል ጨዋታ የሚፈጠሩ ዕድሎችን በተሻለ ትኩረት መጠቀም እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።

ሴኔጋል በአፍሪካ እግር ኳስ ጠንካራ ስም ያለው ቡድን ቢሆንም፣ ዋሊያዎቹ በራሳቸው ሜዳ ወደ ኋላ ብለው የሚጫወቱበት ምክንያት እንደሌለ ዮሐንስ ሳህሌ ገልጸዋል። ተጫዋቾቻቸው ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ለ90 ደቂቃ ተፋልመው ውጤት ለማግኘት ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

የቡድኑ አምበል ያሬድ ባየህ በበኩሉ፣ ብሔራዊ ቡድኑ ለረጅም ጊዜ ጨዋታዎቹን ከሀገር ውጪ በተቃራኒ ቡድኖች ደጋፊዎች ጫና ውስጥ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሷል። አሁን በባህር ዳር በገዛ ደጋፊዎቻቸው ፊት መጫወታቸው ግን ለተጫዋቾቹ ጫና ሳይሆን ትልቅ የስነ-ልቦናና የሞራል ስንቅ እንደሚሆን ገልጿል።

ያሬድ በሱዳን ጨዋታ የታዩትን የታክቲክና የትኩረት ክፍተቶች ለማረም ቡድኑ በስልጠናው ወቅት በቂ ስራ መስራቱን ገልጾ፣ ተጫዋቾቹ በሴኔጋል ጨዋታ ሙሉ ትኩረታቸውን ሰጥተው ውጤት ለማግኘት ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ተናግሯል።

ዋሊያዎቹ ከረጅም የሜዳ ውጪ ቆይታ በኋላ በሀገራቸው እና በደጋፊዎቻቸው ፊት የሚያደርጉት የሴኔጋል ፍልሚያ፣ በ2027 የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ጉዟቸው ውስጥ ጠቃሚ ነጥቦችን ለማሳካት የሚደረግ ወሳኝ የምድብ ጨዋታ ይሆናል።