የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑራ፣ ዋልያዎቹ ከሴኔጋል ጋር ለሚያደርጉት ወሳኝ ጨዋታ በሚገባ መዘጋጀታቸውን ገለጸ።
ከጨዋታው አስቀድሞ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ቆይታ ያደረገው አቡበከር፣ ግብ ጠባቂ ብቻውን ለቡድኑ ውጤት ማምጣት እንደማይችልና እግር ኳስ የቡድን ሥራ መሆኑን ተናግሯል።
ከሱዳን ጋር ባደረጉት ጨዋታ ጥሩ የግብ ዕድሎችን ቢያገኙም መጠቀም እንዳልቻሉ የገለጸው አቡበከር፣ ሱዳን በበኩሏ ያገኘችውን ዕድል በመጠቀም ጨዋታውን ማሸነፏን አንስቷል።
ቡድኑ ሴኔጋልን ከግምት ያስገባ የጨዋታ ዕቅድ መሠረት በማድረግ ልምምዱን ማከናወኑንም ገልጿል። ሴኔጋል ጠንካራ ቡድን ቢሆንም፣ ተጫዋቾቹ በአንድነትና በቁርጠኝነት ከተጫወቱ ማሳካት የማይችሉት ነገር እንደሌለ አቡበከር ገልጿል።
አቡበከር በባህር ዳር ስታዲየም በክለብ ደረጃ ተጫውቶ ቢያውቅም፣ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በዚህ ሜዳ የመጫወት ዕድል እንዳላገኘ ተናግሯል። ኢትዮጵያ ኮትዲቯርን በዚሁ ስታዲየም ማሸነፏንም አስታውሷል።
የባህር ዳር ደጋፊዎች በስታዲየሙ ጥሩ ድባብ በመፍጠርና ብሔራዊ ቡድኑን ለ90 ደቂቃ በመደገፍ የሚታወቁ መሆናቸውን የገለጸው ግብ ጠባቂው፣ በዚህ ሜዳ ለብሔራዊ ቡድኑ ለመጫወት በጉጉት እየጠበቀ መሆኑን ተናግሯል።
